Homeስነ ጽሁፍ
በዝቅታ ውስጥ ያለ ከፍታ
ይመስለናል እንጂ ራስን ከፍ በማድረግና በመኩራራት ውስጥ ትልቅነት የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ ማንም ከፍ ለማለት የሚወድ ቢኖር ዝቅ ይበል” ያለው ዝቅታ ከፍታ ስለሆነ ነው። በልጅነት ከምንጫወታቸው ጨዋታዎቸ አንዱ ሚዛን ነው አንድ ጎኑ ዝቅ ሲል ሌላኛው ጎን ከፍ ይላል ከዚህ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር ራሳችንን ዝቅ ስናደርግ ክብራችን በሌላኛው በኩል ከፍ እንደሚል ነው ራሳችንን ከፍ ስናደርግ ሰው ያዋርድሃል። “ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስ የልባቸውን ኃሳብ ስላወቀ አንድ ትንሽ ልጅ አምጥቶ አጠገቡ አቆመ፤ ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ ይህን ልጅ በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔንም ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል ሁሉ የላከኝንም ይቀበላል። ምክንያቱም ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።” ሉቃስ 9:46-48 የዓለም ግፊትና ጠብ እኔ ልታይ እኔ ልታወቅ እኔ ላግኝ የሚል ነው:: እዚህ ኃሳብ ውስጥ ብዙ ሰዎች ይራኮታሉ በአንጻሩ ግን ዝቅ ብሎ በማገልገል በኩል ባዶ ነው ማንም የለም እዛ ቦታ ላይ ለመክበር እጅግ ምቹ ነው፡፡ ሕፃናት ለዝቅታ ምሳሌ መሆናቸው ልጆች የክብር ወንበርና ኩራት ጉዳያቸው ስላልሆነ ነው። ጌታችንም ይህን ልጅ የሚቀበል ያለው “እኔ የዋኅ በልቤም ትሁት ነኝ” አንዳለ ራስን ዝቅ ማድረግን የሚቀበል ሰው ትሁት የሆንኩትን እኔን ይቀበላል ሲል ነው፡፡ ራስን ዝቅ ማድረግ ማለት ተፈጥሮአዊ በሆነው ማንነታችን ሰው በመሆናችን አይደለም በዚህ ሁሉም ሰው እኩል ነው፡፡ ሁሉም የእግዚአብሔር ልዩ ፍጥረት ነው። በተፈጥሮ አንዱ ከአንዱ አይበልጥም ሌላው ያለው ተፈጥሮአዊ ሀብት ሌላውም አለው፡፡ ራስን ዝቅ ማድረግ ማለት ዝቅ ብሎ ማገልገል ማለት ነው። ራሱን ለሌሎች እንደሚያንስ አድርጎ የሚያገለግል ሰው ከሁሉም ነገር ለመማር ይፈልጋል ታናናሽ ተብለው የተናቁትን አይንቅም እርሱ ከእነዚህ የሚገኘውን ጥቅም ያስባል እነርሱን በማገልገል የሚገኘውን በረከት ያስባል ራሱን ዝቅ ያደረገን ሰው ማንም ዝቅ አድርጎ ቢመለከተው ለእርሱ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም የሥነ ልቦና አማካሪዎች “አንተ ውስጥህ ባልተጎዳበት ነገር ማንም አይጎዳህም” ይላሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን እግራቸውን ዝቅ ብሎ ሊያጥባቸው ባለ ሰዓት ቅዱስ ጴጥሮስ ለመታጠብ አልፈቀደም ነበር ጌታችንም ይህን ካላደረገ ከእርሱ ጋር እድል ፈንታ ጽዋ ተርታ እንደሌለው ነገረው ቀጠለና እንዲህም አለው “እኔ እንዲህ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁም ተዋደዱ” እግዚአብሔር የሚፈልገው በፍቅርና በትህትና እርስ በእርስ እንድናገለግል ነው፡፡ ማገልገል የሁሉ ሰው የተፈጠረበት ዓላማ ነው ያለ አገልግሎት ያልተፈጠረ ሰው የለም ስናገለግል ደግሞ እጅግ ትርፋማና አመርቂ ደስታና እርካታ እንዲሰጠን በዝቅታ ማገልገል አለብን ዝቅ ማለት ከፍ ማለት ስለሆነ፡፡ በለጋ እድሜው በጣም ሀብታም የሆነን አንድ ሰው ቀረብ ብዬ እዚህ ላይ ለመድረስህ እንደ አንተ ትልቁ ምክንያትህ ምንድነው? ብዬ ጠየቅሁት እርሱም “ሥራ አትናቅ ዝቅ ብለህ ሥራ አትኩራራ ያን ጊዜ እንደኔ ትሆናለህ ብዬ አስባለሁ” አለኝ ዝቅ ማለት ራስን ማስናቅ የሚመስለን አለን ነገር ግን ራሳችንን ባልተገባ መንገድ ለማስከበር የምናደርገው ጉዞ የበለጠ ያስንቀናል። ጉዳዩ አንተ በሰው ፊት ላይ ያለህ አክብሮት ሳይሆን አንተ በሰው ልብ ውስጥ ያለህ ክብር ነው፡፡
በመ/ር አልዓዛር ሱፋ
ምንጭ፦ ብሥራት ዘአንቀጸ ብፁዓን መጽሔት
4ኛ ዓመት 5ኛ እትም
ታኅሣሥ 2015 ዓ.ም
የታሪኩ ባለቤት እንዳጫወተኝ
ከጥቂት ዓመታት በፊት በቤተክርስቲያን አገልግሎት ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው በወቅቱ በገጠመው ፈተና ይማረርና የመልቀቂያ ደብዳቤ ለማስገባት ይወስናል። በአንድ ሌሊት ኃሳብ ይህን መወሰኑ ስሜታዊ እንዳያደርገው ስላሰበ ከተረጋጋ ሰው ጋር ልምከርበት ብሎ ብዙ ጊዜ የሚመክሩት አባት ዘንድ ሄደ። ብሶቱን፣ ሸክሙን፣ መገፋቱን፣ በተለይም ከአገልግሎት ባልደረቦቹ ጋር አንድ ሃይማኖት የሌላቸው እስኪመስል አለመግባባታቸውን እየተነተነ እስኪደክመው ሲያወራላቸው በዝምታ አደመጡት። ደብዳቤውንም አሳያቸው። ሲጨርስ እንዲህ አሉት። “ታዲያ ለቤተክርስቲያን አገልግሎትህ ጠዋት ጠዋት የምስጋና ደብዳቤ እንዲጻፍልህ ነው የምትጠብቀው? ለመሆኑ አንተን ሰይጣን ‘ዛሬ ልፈትንህ ነው የመጣሁት እኔ ሰይጣን ነኝ’ ብሎ እንዲነግርህ ትፈልጋለህ? ለመሆኑ ሰይጣን የት ብሎ የሚያገኝህ ይመስልሀል? ጠንቋይ ቤት? ጭፈራ ቤት? እነዚህ ቦታዎች አንተ የለህም፤ ስለዚህ ያለህበት መምጣት ግድ ይለዋል፤ ስለዚህ ጓደኞችህ፣ ባልደረቦችህ ያንተ ሰይጣን ይሆናሉ፤ አንተ ደግሞ የእነርሱ። በማያጣላ ነገር ትጣላላችሁ፤ ትከራከራላችሁ። አብራችሁ ስለምትሠሩት መልካም ሥራ ማሰብን አስረስቶ የሥራ (የአገልግሎት) ቦታችሁ መምጣትን እስክትጠሉ አምቆ ይይዛችኋል። አንድ ሕንጻ ላይ እየዋላችሁ ላለመተያየት ከቢሮአችሁ መውጣትን ትጠላላችሁ። ቀኑን ሙሉ ቢሮ ብትውሉም እንኳን ክት (የተሰበሰበ) አዕምሮ ስለማይኖራችሁ ውጤታማ ሥራ አትሠሩም። አንድ ሃይማኖት የሌላችሁ እስኪመስል በኃሳብ ትለያያላችሁ። አንድ ቦታ ለመድረስ ብትስማሙም በአንድ መንገድ አትስማሙም፤ ልዩ ልዩ አቅጣጫ በመጠቆምና የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክል በመባባል የትም አትሄዱም፤ ካላችሁበት አትንቀሳቀሱም። የመጨረሻው ነገር አንደኛውን መለያየት ነው፤ ልክ እንደ አንተ ውሳኔ! ከአገልግሎት ቦታ መልቀቅ! ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር እዚያ ቦታ ላይ አሰማርቶህ እያለ በነበረበት ወቅት ልትሠራ ትችላቸው የነበሩትን አንኳር ሥራዎች እያሳየ ያመለጠህን እድል ያሳይሃል። ከአገልግሎት ተራራ ከወረድህ በኋላ ስህተትህን ይነግርሃል፤ በመጀመሪያ ላይ የነበረህን ህልም ያሳይሃል…. እንዲቆጭህ ደግሞ ይሠራል፤ ከወርቃማው ዕድልህ ማማ ላይ እንዴት አድርጎ እንዳወረደህ ቁልጭ አድርጎ ያሳይሃል…. ልጄ ቤተክርስቲያን ጠዋት ጠዋት የምስጋና ደብዳቤ አትጽፍልህም። ትጋትህን ተጋድሎህን ግን ትቆጥራለች። የምትከፍለውም ዋጋ ሰማያዊ ነው። በል ልጄ የጻፍከውን የሥራ መልቀቂያም አንብቤዋለሁ፤ በላ እንግዲህ ውሰድና አስገባው!” ቡራኬ ተቀብሎ ሲወጣ አዲስ ሰው እንደሆነ እየተሰማው ነበር። የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤውን ቀዳድዶ ወደ ቅርጫት አስገባውና ወደ መደበኛ ሥራው በአዲስ መንፈስ ተመለሰ።
እሌኒ በርሔ
ምንጭ፦ ብሥራት ዘአንቀጸ ብፁዓን መጽሔት
4ኛ ዓመት 6ኛ እትም
ሐምሌ 2015 ዓ.ም
“ጌታውን ደስ ያሰኘ ታማኝና ቸር አገልጋይ ማነው?” ቅዱስ ያሬድ
በዚህ ዘመን ለምንኖር አገልጋዮች አገልግሎታችንን የሚያዳክሙ ነገሮች ምንድን ናቸው?
፩. የመንፈሳዊ ሕይወታችን መዛል፦ መንፈሳዊ ዝለት በሁለት መንገድ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አንደኛው ያለ አቅም የተጀመረን መንፈሳዊ ተግባር ቀስ በቀስ ማቋረጥና ወደ ቀድሞው ሥጋዊ ሕይወት መመለስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቀስ በቀስ ያደገን መንፈሳዊ ሕይወት የሚጠይቀውን መንፈሳዊ አኗኗር ከመሰልቸት የሚመጣ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ በሕይወቱ ወደ ኋላ የተመለሰ ሰው ለአገልግሎት (ለመታዘዝና ለመታመን) የነበረው ፍቅር ይቀንስና ሁልጊዜ መጸጸትን ብቻ ሥራው ያደርጋል፤ “የነበርኩ” ሕይወትንም ይለማመዳል፡፡
፪. ምቹ ሁኔታዎችን መሻት፦ ሰዎችን መርጦ መታዘዝና ማገልገል ቀላል ነው፤ ሰው ሲመቸው ማገልገል ሳይመቸው ከቤተክርስቲያን መቅረትንም ገንዘቡ ያደረጋል። ነገር ግን እስከ መጨረሻው ጸንቶ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ደግሞ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ሰማዕትነትን መክፈል ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ የአገልግሎትን ጣዕም አንረዳውም፡፡ ”በዝግታ ቆመህ በጊዜውም ያለጊዜውም ቃሉን ስበክ፤ በሁሉም እየታገሥህና እያስተማርህ ገሥጽ፤ ዝለፍ፤ ፈጽመህ አጽናና፤” ያለውን የሐዋርያውን ቃል ማሰብ ጠቃሚ ነዉ፡፡ ፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪
፫. ዓላማን መርሳት፦ መታዘዝም ሆነ መታመን ትርጒም የሚኖረው በዓላማ ሲፈጸም ነው፡፡ ኃላፊነትን መርሳት ከመስመር ያርቀናልና ሁልጊዜ የመጣንበትን ዓላማ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ከተመሠረተው በቀር ሌላ መሠረት ሊመሠርት የሚችል የለም” ብሎ እንደተናገረው መሰባሰባችንን ለሌላ ዓላማ መጠቀምም ሆነ ማሰብ ተገቢ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ፩ኛ ቆሮ. ፫፥፲፩
፬. ባላገለግልም እጸድቃለሁ ብሎ ማሰብ፦ በእርግጥ ለጽድቅ የሚያበቃን የእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ የእኛ በጎ ምግባር ብቻ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ነቢዩ ኤርምያስም “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና” በማለት ተናግሯል። ባላገለግልም እጸድቃለሁ ብሎ ማሰብ ራስ ወዳድነት ከመሆኑም በላይ ድርሻንም አለመገንዘብና አለማወቅም ጭምር ነው፡፡ ባለአንዱ መክሊት ድርሻውን ስላልተወጣ የተፈረደበት ለዚህ ነው፡፡ “በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” በማለት መጽሐፍም ያስረዳናል፡፡ ሰቈ.ኤ. ፫፥፳፪፣ ሐዋ ፲፬፥፳፪
በጎ አገልጋይ ለመሆን ምን እናድርግ?
፩. መታዘዝ፦ የሰው ልጅ በፈጣሪው አርአያና አምሳል ሲፈጠር የሚያዝም የሚታዘዝም ሆኖ ነው፡፡ አገልግሎት (መንፈሳዊነት) መታዘዝ ነው ስንል እንደ ባለ አምስቱና ባለሁለቱ አገልጋዮች ያለምንም ማጉረምረም ከኃጢአት በስተቀር ሁሉንም ተቀብሎ ማከናወን ማለት ነው፡፡ አብርሃም “ልጅህን ሠዋልኝ” የሚለውን የእግዚአብሔርን ጥያቄና ትእዛዝ የተቀበለው በጸጋም በደስታም ነው፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያት ኃላፊውን ዓለም በማይታየው ዓለም ለውጠው መንፈሳዊ ተልእኮን እንዲወጡ ለእግዚአብሔር ቃል ሲታዘዙ በደስታ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም የአባቶቻችንን መታዘዝ መታዘዛችን ልናደርግ ይገባናል።
፪. በትጋት ማገልገል፦ ከዘመነ አበው ጀምሮ የእግዚአብሔር ወዳጆች እየተባሉ የሚጠሩ ሁሉ የፍቅረ እግዚአብሔር መገለጫቸው ትጋታቸው ነበር፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት ከትጋት ውጭ መለኪያ የለውም፡፡ ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተመረጡት ከሥራ ቦታቸው ነው፡፡ ጌታችን ሲመርጣቸውም እጅግ በጣም ትጋትን ለሚጠይቅ ተልእኮ ነበር፡፡ ዋጋን ለመቀበል ከጠዋት እስከ ማታ በአገልግሎት መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም በምሳሌ “በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው” በማለት ትጋት የመንፈሳዊ ዋጋ መጠበቂያ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ማቴ. ፲፥፩-፲፬፣ ፳፥፩-፲፪፣ ምሳ ፲፰፥፱
፫. በተስፋ የተመላ ትጉህ አገልጋይ መሆን፦ የሰው ልጅን በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወት የሚመሩ የእግዚአብሔር ወዳጆችን ከሌላው ሥነ-ፍጥረታት የተለዩ የሚያደርጋቸው ተስፋ ነው፡፡ የተወለደው የማደግ ተስፋ፣ ያደገው የመኖር ተስፋ፣ በኃጢአት የወደቀው በንስሓ የመነሣት ተስፋ፣ ቤተክርስቲያንን የማገልገል ተስፋ፣ መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ ተስፋ ለሰው ልጆች በተለይም ለእኛ ለክርስቲያኖች የተሰጠን ተስፋችን ነው፡፡ ነቢያትን በትንቢት ያጸናና መከራውን እንዲታገሡ ያደረጋቸው፣ ሐዋርያትን በሐዋርያነት ያጸናና በሰማዕትነት ያጠነከራቸው፣ ከዘመነ አበው እስከ ዕለተ ምጽአት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስተሳስሮ የሚኖር ኅቡእ ሰንሰለት ተስፋ ነው፡፡ አባቶቻችን “የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን” ሆኖ መገኘት የግድ ነው፡፡ በአጠቃላይ እኛም ኦርቶዶክሳውያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ነግደን እንድናተርፍበት ከጌታችን የተሰጠንን መክሊት በግዴልሽነት፣ በትዳር፣ በትምህርትና በቦታ ርቀት ምክንያት አንዳችን ከአንዳችን ባለመስማማት ለራሳችን ሰበብ እየፈጠርን እንደ ባለአንዱ አገልጋይ ከቀበርነው ቆይተናል፡፡ ጌታችንም የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ስለማናውቅ ከቀበርንበት አውጥተን ልናተርፍበት ይገባናል። “እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን ዛሬ ነው” እንዳለ ሐዋርያው አትርፎ መገኘት ለእኛ ለክርስቲያኖች የግድ ያስፈልገናል፡፡ ፪ተኛ ቆሮ. ፮፥፪ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “መኑ ውእቱ ገብርኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ፤ በጎ ሥራ እየሠራ ጌታው ያገኘው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማነው?” እንዳለ ታማኝነትና መታዘዝ ከሌለን፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ከራቅን፣ በጌታችንም ፊት መሾም መሸለም፣ ወደ ዘለዓለማዊ ደስታ መግባት አይኖረንም፡፡ ስለዚህ በተሰጠን ስጦታ፣ ሀብት፣ አቅም፣ ጊዜ፣ ቦታና ዕድሜ ስጦታውን ለሰጠን እግዚአብሔር ታምነንና በአገልግሎት ጸንተን ወጥተው ወርደው አትርፈው ከተሾሙት ወገን እንዲደምረን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይፍቀድልን፤ አሜን።
በዲያቆን ግዛው ቸኮል
ምንጭ፦ ብሥራት ዘአንቀጸ ብፁዓን መጽሔት
6ኛ ዓመት 9ተኛ እትም
ታኅሣሥ 2017 ዓ.ም