gettyimages-667609663-612x612

ትሕትና ምንድር ነው?

ትሕትና ምንድር ነው? ብዙ ጊዜ በእኛ ዘንድ የተናቀ ልብስ መልበስ ፣ አንገት መስበር ፣ ዝግ ብሎ ማውራት እና ‹እኔ በደለኛ የማይገባ ሰው ነኝ› እያሉ ደጋግሞ መናገር እንደ ትሑት ያስቆጥር ይሆናል፡፡ ነገር ግን የትሕትና ትርጉም ከዚህም በላይ ነው፡፡ በርግጥ ከላይ የዘረዘርናቸው ነገሮች የአንድ ትሑት ሰው ከፊል መገለጫ ጠባያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን በማድረግ ብቻ ትሑት መሆን ቢቻል ኖሮ ፤ በዓለም ላይ ያለው የትዕቢተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ትሕትናን በተጠቀሱት ውጫዊ ምግባራት ብቻ የምንረዳው ከሆነ ከእውነተኛ ትርጉሙና ማንነቱ እንዳናሳንሰው ስጋት አለኝ፡፡

ትሕትና በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ እውነተኛ ኑሮ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ስለ ትሕትና ሲያስብ እነዚህን ሁለት ነገሮች አብሮ በትኩረት ሊያሰላስል ይገባዋል፡፡ እነርሱም አንደኛ ተፈጥሮውን (መሬታዊ ፣ትቢያ መሆኑን) አለመዘንጋት ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ተቀባይነቱን ለዘወትር ማስታወስ ነው፡፡ ሰው በጫማው እየረገጠ የሚራመደው አፈር እንደሆነ ሲያስብ ደካማነቱን ይረዳል፡፡ ስለዚህም በነገሮች ሁሉ ‹አቤቱ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ› እያለ ረድዔተ እግዚአብሔርን የሚማጸን ትሑት ይሆናል፡፡ (መዝ 103፡14) ተቀባይነቱንም ሁል ጊዜ የሚያስታውስ ከሆነ ለሌሎች በሚያደርጋቸው በጎ ሥራዎች አይኩራራም፡፡ ብልጫም አይሰማውም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ሳይሆን ከአምላኩ ከተሰጠው ላይ ቀንሶ የሚያካፍል ምስኪን ምጽዋተኛ ስለሆነ፡፡ ሐዋርያውስ ቢሆን በቆሮንቶስ መልእክቱ በታላቅ ቃል ‹አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለምንድር ነው?› ሲል የሚገስጸው ስለዚሁ አይደለምን? (1ኛቆሮ 4፡7)፡፡

ሶርያዊው አባት ማር ይስሐቅ ስለ ትሕትና ትርጉም አንድ ቁም ነገር ያካፍለናል፡፡ ምን አለ? ‹ውድቀትና ኃጢአቱን እያነሣ ራሱን የሚወቅስና የሚያዋርድ ጥሩ ቢያደርግም ትሑት ተብሎ ግን አይጠራም፡፡ ትሑት ሰው ራሱን ማሳመንና ኅሊናውም ይህን ሐሳብ እንዲይዝ መጫን አይጠበቅበትም፡፡ እንዲሁ ራሱን ምንም አድርጎ ይቆጥራል እንጂ› ሲል አስተማረ፡፡ እንደ ማር ይስሐቅ ትምህርት ከሆነ ትሑት ለመሆን ሲባል ራስን ማስጨነቅ ወደ ትሕትና ጫፍ ለመድረስ ሯጭ(ተጋዳይ) መሆንን የሚያሳይ እንጂ ‹ትሑት› አያሰኝም፡፡ እውነተኞቹ ትሑታን ሌላ የሚጋፋ እና ትግል የሚጠይቅ አንዳች የበላይነት (የእኔነት) ስሜት ሳይሰማቸው እንዲሁ ራሳቸውን የሰው ሁሉ መጨረሻ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ባሕታዊም ‹ትሑት ሰው የሚባለው ራሱን የሚሰድብና የሚያዋርድ ሳይሆን ፤ ከሌሎች ሰዎች በሚደርስበት ስድብና ትችት ፊት ፍቅሩ ሳይቀንስበት መቆም የሚችል ሰው ነው› በማለት ያስተማረው ይህን የፍጹማኑን ትሕትና ለማሳየት ነው፡፡

አባ መቃርዮስ እንደተናገረ የትሕትና ተቃራኒ የሆነች ትዕቢት የኃጢአቶች ሁሉ ራስ (እናት) ናት፡፡ ታዲያ ትዕቢት ለኃጢአቶች ሁሉ እናት ከሆነች ትሕትና ለጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ራስ ብትሆን ምን የሚያስደንቅ ነገር አለ?!፡፡ ለዚህም ነው እኮ ቅዱሳን አበው ትሕትናን ‹እጸ ሕይወት›/‹የሕይወት ዛፍ› እያሉ የሚጠሯት፡፡ አዳም በገነት አንድ ሺ ዓመት ከኖረ በኋላ ወደማታልፈው መንግሥት (መንግሥተ ሰማያት) ለመግባት የሚታደስባትን እጸ ሕይወት አምላኩ በገነት ዛፎች መካከል ፈጥሮለት ነበር፡፡ እርሱም ትእዛዘ እግዚአብሔርን ጠብቆ ሺ ዘመን ቢቆይ ኖሮ ፤ ላይወድቅ ላይጎሰቁል በእጸ ሕይወት ታድሶ መንግሥተ እግዚአብሔርን ይወርስ ነበር፡፡ ከእጸ ሕይወት በኋላ መውደቅ የለምና፡፡ እንዲሁ ትሕትናም እጸ ሕይወት ነች፡፡ ትሕትናን ገንዘብ ካደረጉ በኋላ ውድቀት እና ከእግዚአብሔር መለየት የለም፡፡

ትሕትና በጎ ሥራዎች ሁሉ የሚጠበቁባት አጥር ቅጥር ነች፡፡ ከእግዚአብሔር የምናገኛቸው ጸጋዎችም ያለ ትሕትና ሊጸኑ ፣ ሊሰነብቱ አይችሉም፡፡ ቅዱሳን በጽኑዕ ተጋድሎ እና በፈጣሪ ቸርነት የገነቡትን የጸጋ ግንብ ሰይጣን እንዳያፈርስባቸው ፈጣሪያቸው የሚከላከልላቸው ትሑታን የሚሆኑበትን ደዌ ወይም አንዳች ነገር በእነርሱ ላይ በማምጣት ነው፡፡ ባለ ብዙ ጸጋ የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የእግዚአብሔር አሠራር ሲያስረዳን ‹በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ…ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው› በማለት ግልጽ አድርጎ ይናገራል፡፡(2ኛ ቆሮ 12፡7) በሰውነቱ ጥላ እና በልብሱ እራፊ ሙት የሚቀሰቅሰው ፣ሕሙም የሚፈውሰው ሐዋርያ እንደ ስንጥር በሚወጋ ራስ ምታት መያዙ ፤ ተአምር ሲያደርግ በተመለከቱት ሰዎች በስህተት እንዳይመለክና ልብን ሰቅዞ በሚይዝ አጉል ውዳሴ እንዳይጠለፍ አድርጎታል፡፡ በርግጥም የገባሬ ተአምራት የቅዱስ ጳውሎስን ሕመም ያዩ ሰዎች በእርሱ ድካም ውስጥ የሚሠራ የእግዚአብሔርን ኃይል በግልጽ ተረድተዋል፡፡

እግዚአብሔር በጎውን ዋጋ የሚሰጠን መልካም ስላደረግን ይመስላችኋል? አይደለም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ መልካም የሚያደርጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር በጎውን ዋጋ ላይቀበሉ ይችላሉ፡፡ ለምን? ከአምላክ ዘንድ በጎ ዋጋ የሚያሰጠው መልካም ማድረግ ሳይሆን ፤ መልካሙን ነገር በትሕትና ማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ከተነሡ ውዝግቦች (ክህደቶች) መካከል አንዱ የሆነው የ‹Pelagius controversy› ለዚህ ጉዳይ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የአየርላንድ መነኩሴ በሆነ ፔላጊዮስ የተጠነሰሰ ሲሆን ፤ አጠቃላይ ምልከታውም ‹ሰው ብቻውን በሚያደርገው በጎ ሥራ ይድናል› የሚል በረድዔተ እግዚአብሔር መደገፍንና ትሕትናን አውልቆ የሚጥል የክህደት ትምህርት ነበር፡፡ በእውነትም የማታልፍ የማትለወጥ የእግዚአብሔርን ርስት ፣ ፈራሽ በስባሽ በሆነው ሰውነቴ ብቻ ሠርቼ ገንዘብ አደርጋለሁ ከማለት በላይ ተሻለ ክህደት ከወዴት ሊመጣ ይችላል?

እስኪ ጽሑፋችንን በቅዱስ መቃርስ ምሳሌ እንዝጋው፡፡ አባ መቃሪ በአንድ ወቅት ስለ ትሕትና ሲያስተምር ‹አንድ ባለጠጋ የነበረ ንጉሥ ያለውን ሀብት በአደራ መልክ ከአንድ ደሃ ዘንድ ቢያኖር ፤ ያ ደሃ በእነዚያ ብሮች እና ወርቆች ሊመካ ይችላልን? እንደ ራሱ ንብረትስ በመቁጠር የባለቤትነት ስሜት ሊሰማው ይገባል?› ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ቅዱስ አባት ምሳሌ መሠረት ያ ባለጠጋ ንጉሥ እግዚአብሔር ነው፡፡ አደራ ተቀባዩ ነዳይ ደግሞ እኛ ነን፡፡ አደራውም በእጃችን ያሉ በጎ ነገሮች ሁሉ ናቸው፡፡ ያሉንን መልካም ነገሮች እንደ ራስ ንብረት መቁጠርና በሌላው ላይ መኩራራት አደራ ተቀባይነትን እንደ መርሳት ነው፡፡ ሰው ባልፈጠረው በጎነት እንዴት ይኩራራል?

በትሑታኑ ቅዱሳን ጸሎት ይጠብቀን!

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
selam@dnabel.com
አዲስ አበባ

ድረ ገጹን ይጎብኙ
https://dnabel.com

Tags: No tags

One Response

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *