ተአምረኛው ሕፃንና እናቱ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? እረፍት እንዴት ነው? የዚህን የሁለት ወር ክረምት እረፍታችሁን እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? ልጆች ቤተሰባችሁን በመላላክ ሥራ በማገዝ እያገለገላችሁ ነው? በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲያን ተገኝታችሁ ትምህርት ቃለ እግዚአብሔርን በሰንበት ትምህርት ቤት በመማር በዝማሬ እግዚአብሔርን እያመሰገናችሁ ነው? እንደዚህ ከሆነ በርቱ እሺ እግዚአብሔር የሚወደው እንደዚህ ዓይነቱን ነው፡፡
ልጆች ዛሬ ሐምሌ 19 የሚከበረውን ቅዱስ ገብርኤል ስላዳናቸው አንድ እናትና አንድ ልጅ ታሪክ አዘጋጅተንላችኋል በትዕግስት ተከታተሉን እሺ፡፡ የሕፃኑ ስም ቅዱስ ቂርቆስ ሲሆን የእናቱ ስም ደግሞ ቅድስት ኢየሉጣ ትባላለች አባቱ ቆዝሞስ ይባላል፡፡ ሐገሩ ሮም አንጌቤ ነው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ የተባለ ንጉሥ በነገሠበት ጊዜ በ 303 ዓ.ም. አብያተ ክርስቲያናትን ማፈራረስ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ መሰደድ ጀመሩ፡፡ ከእነዚህም መሐል የ 3 ዓመት ሕፃን የያዘች እናት ነበረች እናትየዋም ልጇን ይዛ ኢቆንዮን ወደ ተባለ ሐገር ሸሸች የሐገሩ መሪ ባለሥልጣኑ እለእስክንድሮስ ክርስቶስን ካጂ ለጣዖት ስገጂ አላት እናትየውም ዓይን እያለው ለማያይ ጆሮ እያለው ለማይሰማ በቃልህ አዘህ በእጅህ ሠርተህ ላቆምከው ምስል አልሰግድም አለች፡፡ አይሆንም ካልሽማ በሰይፍ ትቀጪያለሽ ብሎ አስፈራራት ሕፃኑን ወርቅ እሰጥሃለሁ ለዚህ ጣዖት ስገድ አለው፡፡ ልጆች እስቲ እናንተን ወርቅ እሰጣችኋለሁ ክርስቶስን ካዱ ብትባሉ ምንድነው መልሳችሁ? እሺ ብሎ መስገድና ወርቅ መውሰድ ነው? አይደለም አይደል፡፡ ወርቅን የፈጠረው ማነው? ወርቅን ብቻ ሳይሆን ይህንን ዓለም የፈጠረ ማን ነው? ክርስቶስ ወይም እግዚአብሔር አይደል፡፡ ልጆች የሦስት ዓመት ሕፃኑ የመለሰለትን መልስ እንመልከት። መንፈስ ቅዱስም አድሮበት ስለነበር “ራሳቸውን እንኳ ማዳን ለማይችሉ ርኩሳት ጣዖታት አልሰግድም” አለው ይህ ሕፃን የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ስላደረበት ነው፡፡ እኛም መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርብን በቤተክርስቲያን ቃለ እግዚአብሔር መስማት፣ መዘመር፣ ታላላቆቻችንን ማክበር፣ ለወላጆቻችን መታዘዝ ያስፈልጋል እሺ ልጆች፡፡ የፈላው ውኃ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይሰማ ነበር፡፡ ሊከቷቸው ሲወስዷቸው እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ልቧ በፍርሐት ታወከ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን ፍርሃቷን አርቅላት እያለ ይፀልይላት ነበር፡፡ ልጆች አያችሁ እግዚአብሔር የሕፃን የትልቅ የወጣት የሴት የወንድ አይልም በአንድ መንፈስ በቅን ልቡና በተሰበረ ልብ ሆነው ቢጸልዩ ይቀበላል፡፡ እናንተም ስለቤተሰባችሁ ስለ ሀገራችሁ ልትጸልዩ ይገባል እሺ፡፡ እንደውም ሕፃኑ እናቱን “አትፍሪ አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን ያዳነ እኛንም ያድነናል” እያለ እያበረታታ ልብሷን እየጐተተ እርሷም ጨክና ተበረታታ በእሳት በፈላው ውሃ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ በበትረ መስቀሉ እሳቱን እጥፍቶ የፈላውን ውሃ አቀዝቅዞ አውጥቷቸዋል። በወጡም ጊዜ ልብሳቸው ሳይለበለብ፤ ሰውነታቸው ሳይሸበሸብ፤ ምንም የፈላ ውሃ ውስጥ የገቡ ሳይመስሉ ወጥተዋል፡፡ ከአሕዛብ የሚያምኑ ከነበሩ ብዙዎች በእግዚአብሔር አምነው ተጠምቀዋል።
ከቅዱስ ቂርቆስና ከእናቱ ከቅድስት ኢየሉጣ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡
በማስተዋል እንዳነበባችሁ ለማወቅ እስቲ ጥያቄ እንጠይቃችሁ?
1.ሕፃኑ ቂርቆስ ሀገሩ የት ነው?
መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርብን ምን እናድርግ?
ቅዱስ ገብርኤል ከፈላው ውሃ ያዳናቸው መቼ ነው?
ቅዱስ ቂርቆስ ምሳሌ አድርጎ የጠራቸው እንደነ እርሱ ያድነናል ያላቸው እነማን ናቸው?
የቅዱስ ቂርቆስ እናት ስሟ ማነው?