ትምህርት

እንግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፡፡

ማቴ 28፥19

  “እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤ ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጓልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፡፡” ሉቃ 1፥48-49

 ይህ ቃል የተወሰደው የማርያም ጸሎት ተብሎ ከሚታወቀው ከሉቃስ ወንጌል ክፍል ውስጥ ነው። ጸሎቱ በትሕትና የተሞላ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀንሳ እንደምትወልድ በመልአኩ ብሥራት ከተነገረላት በኋላ ራሷን ዝቅ አድርጋ “የባርያውን ትሕትና ተመልክቶአልና፤…” ሉቃ. 1፡48 ስትል ነው የምናገኛት፡፡ የአምላክ እናት መሆን ከክብር በላይ የሚልቅ ታላቅ ክብር ነው፡፡ “እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤” ብላ በሙሉ መንፈስና ልብ እንድትናገር ያደረጋት ይህ ታላቅ ክብር ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ናት እያለች የምትናገረው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ለእርሷ የተሰጣት ክብር ለማንም አልተሰጠም፡፡ ስሙ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በእርሷ ታላቅ ሥራ ስላደረገ ነው ትውልድ ሁሉ ከዚያች ዕለት አንሥቶ ብፅዕት እያለ እንደሚጠራት የተናገረችው። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ድንቅ በሆኑ ቃላት አምላክን እንደምትወልድ ሲያበሥራት በትሕትና ተሞልታ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል” ሉቃ 1፡34 የሚል ጥያቄ አቀረበችለት እንጂ ፈጥና ብሥራቱን አልተቀበለችም፡፡ መልአኩም ሳይታክትና ሳይሰለች ለዘመናት መካን ተብላ ትጠራ የነበረችው ዘመዷ ኤልሳቤጥ በእርጅናዋ ጊዜ ወንድ ልጅ ከፀነሰች ስድስት ወር እንደ ሆናት አስረግጦ ነገራት ሉቃ 1፡36፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ በላይ ልትሄድ ስላልቻለች አንድ ቃል ብቻ ተናገረች “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ … እነሆኝ የጌታ ባሪያ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ።” ሉቃ 1፡37 ዓለሙ ሁሉ ፍጹም በረከሰበትና በተበላሸበት ዘመን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስን በማኅፀኗ ለመፀነስ ብቁ ሆና የተገኘችው እርሷ ብቻ ናት፡፡ ቅዱስ ሉቃስ “የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር፡፡” ሉቃ.1፡27 ብሎ ስለ ተናገረ ፍጹም ድንግልናዋን አረጋግጦልናል። ቅድስናዋን፣ ድንግልናዋን፣ ታላቅነቷን፣ ትሕትናዋን፣ ጸጋ የሞላባት መሆኗን፣ ጌታ ከእርሷ ጋር መሆኑን፣ እርሷ ከሴቶች ሁሉ መካከል የተባረከች መሆኗን ካወቅን በኋላ፣ በጸሎቷ ውስጥ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ማድረጓን ከተረዳን በኋላ፣ መልአኩን እንዲህ ብለህ አብሥራት ብሎ እግዚአብሔር ከላከውና ካበሠራት በኋላ ነው “እነሆም ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤” ሉቃ.1፡ 48 ብላ የተናገረችው፡፡ “ትውልድ ሁሉ” የሚለው ቃል የሚያመለክተን ከትውልድ ሐረግ ውስጥ ገብቶ የሚቆጠር የሰው ልጅ ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አንቺ ብፅዕት፣ ንዕድ፣ የተባረክሽ ብሎ ከልቡ ቢያመሰግናት ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም፤ ይከብራል እንጂ አይዋረድም፡፡ በእግዚአብሔር፣ በቅዱስ ገብርኤልና በትውልድ ሁሉ የተቀደሰችና የተከበረች ድንግል እናታችንን በጸሎታችን፣ በመዝሙራችን፣ በቅዳሴያችን፣ በማኅሌታችን፣ በሰዓታታችን፣ በማኅበራችን፣ በጠበል ጠዲቃችን፣ በምጽዋታችን፣ በጾማችን ስሟን እያመሰገንን ብንጠራትና አማላጅነቷን ከልባችን ብንቀበል እኛም እንከብራለን እንጂ የሚጠፋብን ነገር አይኖርም፡፡ በወንጌል እግዚአብሔር ያከበራቸውን ታናናሽ ቅዱሳንን ሁሉ እኛም አክብረን ብንቀበላቸው ዋጋችን እንደማይጠፋብን እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡” ማቴ 10፡40-42 በዚህ ጥቅስ መሠረት የእግዚአብሔር ሰዎች የሆኑትን ተቀብሎ በስማቸው ዳቦ፣ እንጀራ፣ ቆሎ ቢያበላና ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ቢያጠጣ ወደፊት በሰማይ የሚያገኘውን የመንግሥተ ሰማያት ዋጋ አያጣም ማለትም ዘላለማዊ ሕይወትን አያጣም ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች በቅዱሳን ስም በሚያቋቁሟቸው የጽዋ ማኅበራት ውስጥ የሚያመሰግኑት፣ የሚያወድሱትና ከፍ ከፍ የሚያደርጉት እግዚአብሔርንና የእርሱን ወዳጆች ነው፡፡ በእነርሱ ስም ቢያበሉ፣ ቢያጠጡ፣ ቢመጸውቱ፣ ቢጾሙ፣ በጎ ነገር ቢያደርጉ፣ ቢያሸብሽቡና ስማቸውን ከእግዚአብሔር በታች ቢያገንኑ ዋናውን የመንግሥተ ሰማያት ዋጋ ያገኛሉ እንጂ አይጎዱም ማለት ነው፡፡ የእመቤታችን ዘመድ ወይም አክስት የሆነችው ቅድስት ኤልሳቤጥ እርሷን ብፅዕት ብላ በመጥራቷ አልተጎዳችም፡፡ ይልቁንም ቅዱስ ገብርኤል እንዳወደሳት ከእርሱ በመማር እንዲህ ብላ አወደሰቻት እንጂ፡፡ ኤልሳቤጥ ድንግል ማርያምን እንዴት እንዳመሰገነቻት ቅዱስ ሉቃስ በወንጌል እንደሚከተለው አስፍሮልን እናነባለን “ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፤ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች፡- አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘልሎአልና። ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት፡፡” ሉቃ 1፡41-45፡፡ ይህ ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ፤ ውስጥ የተጠቀሰ መንፈሳዊ ቃል ነው እንጂ ተረት ተረት አይደለም፡፡ ወንጌል ደግሞ የእግዚአብሔር፤ የክርሰቶስና የመንፈስ ቅዱስ ወይም የአብ፤ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ወይም የሥላሴ ቃል ወይም የእስትንፋስ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ደግሞ በሥላሴ ቃል ልንመራ ግድ አለብን፡፡ በዚህ መሠረት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለእኛ ሰላምታ ስትሰጠን እንደምትባርከን፣ በመንፈስ ቅዱስ እንደምንቃኝ፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ እንደምንላት፣ የማኅፀንዋ ፍሬ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም የተባረከ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ሰው ልክ እንደ መጥመቁ ዮሐንስ እናት እንደ ኤልሳቤጥ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና መድኃኔዓለምን አንድ ላይ ለማወደስ ይነሣሣል እንጂ አይነጣጥልም። በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ድንግል ማርያም ከተወዳጁ ልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብራ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) የምትሣለው ለዚህ ነው፡፡ በብሥራቱ፣ በፅንሰቱ፣ በልደቱ፣ በመዋዕለ ስብከቱ፣ በመከራው፣ በሥቃዩ፣ በስቅለቱ፣ ነፍሱን በመለየቱ፣ በሞቱ፣ በመቃብሩ፣ በትንሣኤውና በእርገቱ ከእርሱ አልተለየችም፡፡ ስለዚህ ይህ ሥዕል ድንቅ ምሥጢር ያዘለ መሆኑን ክርስቲያኖች ሁሉ ልብ ሊሉት ይገባቸዋል፡፡ ድንግል ማርያም ሰላምታ ስትሰጥ መንፈስ ቅዱስን የምታሳድር ከሆነ ወደ እርሷ መቅረብ አንጂ ከእርሷ መራቅ፣ እርሷን ማጥላላትና እርሷ ወደሌለችበት መኮብለል ከኃጢአት ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ ምናለ እኔ ከልቤ ቀርቤያት በሰላምታዋ እግዚብሔር መንፈስ ቅዱስን ብታሳድርብኝ!?! መንፈስ ቅዱስ አደረብኝ ወይም ቀረብኝ ማለት ደግሞ ኃጢአት ከእኔ ራቀ ማለት ነው፡፡ ድንግል ማርያም ከአብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ ግንኙነት እንዳላት በዚህ እናውቃለን፡፡ ከምንም ነገር በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ዓለም ያዳነው ከእርሷ በነሣው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ቤተክርስቲያናችን እርሷን “የድኅነታችን ምክንያት” ወይም “ምክንያተ ድኂን” ብላ የምትጠራት ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሚወዳቸው ቅዱሳን ድንቅ ስጦታዎች እንደ ሰጣቸው ስንመለከት እጅግ እደነቃለሁ፡፡ አሁን ለምሳሌ፡- ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ የሚል ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል፡፡ “እውነት እላችኋለሁ እናንተ የተከተላችሁኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክበሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፡፡” ማቴ 19፡28፡፡ ሌላ እንጨምር፡፡ “እውነት፤ እውነት፤ እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፣ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፣ …” ዮሐ.14፡12፡፡ ቅዱሳኑ የእግዚአብሔር ሰዎች በሰዎች ላይ ዘላለማዊ ፍርድ መስጠት የሚችሉና ጌታ የሚያደርገውንና ከዚያም የሚበልጠውን ሥራ መሥራት የሚችሉ ከሆነ እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከዚህ ዝቅ ያለ ሥልጣን ሲሰጣቸው አንዳንዶች ማጉረምረማቸውና መቃወማቸው ያስደንቀኛል፡፡ አንድ ሰው ለራሱ፣ ለሌላው ሰውና ለኃጢአተኛው ሰው በእነዚህ ቅዱሳን ሰዎች ስም ምልጃ ቢያቀርብ ይበልጣል ወይስ በሰዎች ላይ ቢፈርድ? በእነርሱ ስም ጠበል ጠዲቅ አድርጎ ለተቸገሩት ቢረዳ፣ ቢያበላ፣ ቢያጠጣና ቢመጸወት ነው የሚከብደው ወይስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሠራው ሥራ እስከ ዘለዓለም ድረስ እፈርዳለሁና ኢየሱስ ክርስቶስ ከሠራው ሥራ አስበልጬ እሠራለሁ ብሎ ሊሟገት የሚችለው? ሥልጣኑ ቢሰጠንም እንኳ የሚከብድ ከሚመስለን ሥልጣን ይልቅ የሚቀለን የሚመስለንን ሥልጣን ብንይዝ የሚበጀን ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻም የተባረከችውንና የተቀደሰችውን እናታችን ድንግል ማርያምን የሚወዱና ብፅዕት የሚሏት ሰዎች ብዙ ስለሆኑ ብዙ ስሞች እንዳወጡላት እንመለከታለን፡፡ ስሞቿ በቁጥር ሲሰፈሩ መቶ ሃያ ይደርሳሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ኪዳነ ምህረት፣ ማኅደረ መለኮት፣ እመ ብዙኃን፣ ንፅሕተ ንጹሐን፣ ቤተ ሃይማኖት፣ እመ ብርሃን፣ የአዳም ተስፋ፣ የነቢያት ትንቢት፣ የሐዋርያት ሞገስ፣ ምልዕተ ውደሴ፣ ደግሚት ሰማይ . . . ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ሁሉም የእርሷ ስሞች ስለሆኑ በስሞቿ የሚዘከሩትን ዝክሮችና የሚዘጋጁ ጠበል ጠዲቆች ትቀበላለች፡፡ እንደ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅም ትባርከናለች፡፡

እኛም እንደ አዘዘችን ብፅዕት እያልን እናመሰግናታለን፤ ከትውልድ እንድንቆጠር እንሻለንና፡፡ይቆየን፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ የሆነውን ነገር ሁሉ እንዲያሳስበንና እንዲያስፈጽመን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

መ/ር አያሌው ዘኢየሱስ

ምንጭ፦ ብሥራት ዘአንቀጸ ብፁዓን መጽሔት

5ኛ ዓመት 7ኛ እትም

ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም

                                                             

ያንብቡ
ይመልከቱ
Shopping Basket