about-us-cropped

የአንቀጸ ብጹአን ሰንበት ት/ቤት አመሠራረት ታሪክ

ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት የተመሠረተው ጥቅምት 4 ቀን 1959 ዓ.ም ሲሆን በጊዜውም የነበረው ስያሜ የብሥራተ ገብርኤል ወጣቶች መንፈሳዊ ማኅበር የሚል ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዓላማው “ሰው በእህል ብቻ አይኖርም በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ” ማቴ 4 ፥ 4 ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተነገረው ቃለ እግዚአብሔር ምግበ ነፍስ ምግበ ሥጋ እንደመሆኑ መጠን በዕለተ ሰንበት የሰንበት ትምህርት ከሚያስፈልጋቸው ተገልጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት ወጣቶችና ሕፃናትን ለማስተማር ነበር፡፡

ማኅበሩም እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በመሆን ሕልውናውን ለማቆየት ታግሏል፡፡ ከነዚህም መካከል በወቅቱ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው ሥርዓት የእምነት ተቋማት ውስጥ የነበሩ ወጣቶች ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመግባት የራሳቸውን አስተምህሮ ለማራመድ መሞከራቸው ነበር፡፡

በዚህም በማኅበሩ ስም የተለያዩ የወጣት ስብስቦችን በመፍጠር ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ውጭ እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም የፕሮቴስታንትና የጂሆቫ እምነት ተከታዮች በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ምዕመናንን በመረበሽ ማኅበሩ በከባድ ፈተና ውስጥ እንዲያልፍ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በ 1968 ዓ.ም በወርሃ ሚያዚያ አባ ዘሊባኖስ ፈንታ (አሁን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ) የደብሩ አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት ነበር ማኅበሩ ወደ ዐዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረው፤ ይኸውም አባ ዘሊባኖስ ከካህናተ ቤተክርስቲያን፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤና ከአካባቢው ወጣቶች፣ እንዲሁም ከቀበሌው ሊቃነ መናብርት ጋር በመሆን ስለ ወጣቶቹ አቋም ሰፋ ያለ ምክክር አካሄዱ፡፡ ከውይይቱ በኋላም ማኅበሩ በወቅቱ መተዳደሪያ ደንብ ስላልነበረው፣ ያንን እንዲያዘጋጅ በጊዜው ለነበሩት አገልጋዮች ለዲያቆን ወዳጅ ተበጀ (አሁን ቀሲስ) እና መሪጌታ ዓለማየሁ ደስታ ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡

                  በመሆኑም ኃላፊነት የተሰጣቸው መሪጌታ ዓለማየሁ ደስታና ቀሲስ ወዳጅ ተበጀ ኃላፊነቱን በመውሰድ ከውይይቱ እንደተመለሱ ሌሊቱን ሙሉ 24 አንቀጽ የያዘ የመተዳደሪያ ደንብን በማርቀቅ ሚያዚያ 16 ቀን 1968 ዓ.ም ጠዋት ከቅዳሴ በኋላ 3 ሰዓት ሲሆን እነ፡-

አባ ዘሊባኖስ ፈንታ የደብሩ አስተዳዳሪ (አቡነ መርቆሪዎስ)

ቄስ ገ/ሐና ወ/አገኘው(ርዕሰ አበው)

ቄስ ገላው እጅጉ

ቄስ ጥላሁን ማስረሻ

ቄስ ወዳጅ ተበጀ

ዲ/ን ተስፋ መብራቱ

መሪጌታ አለማየሁ ደስታ

            በአንድ ላይ በመሆን ሰንበት ትምህርት ቤቱ በመርህና በመተዳደሪያ ደንብ እንዲመራና ሰርገው እየገቡ ያሉትን አጽራረ ቤተክርስቲያንን ለመቋቋም በማሰብ ሕግና ደንቡን (መተዳደሪያውን) በዲ/ን ወዳጅ ተበጀ አማካኝነት በአዳራሹ ለተገኙ አባላት ተነበበ፡፡ በአዳራሹም ተቀላቅለው የነበሩ መናፍቃን መተዳደሪያ ደንቡን አንቀበልም የደብሩንም አስተዳደር አናውቃችሁም በማለት በይፋ ተለይተው ወጡ፡፡ በዚያኑ ዓመት በወርሃ ግንቦት 28ኛው ቀን 28 ወጣቶች በመሆን ማኅበሩን ዳግም በመመሥረት ስሙንም ቀድሞ ከሚጠራበት የብሥራተ ገብርኤል ወጣቶች መንፈሣዊ ማኅበር ከሚለው አሁን ሰንበት ትምህርት ቤቱ ወደሚጠራበት ስያሜ በመለወጥ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤት በማለት መንፈሣዊ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ ከዚያን ቀንም ጀምሮ በመርሕና በደንብ መመራቱን ቀጠለ፡፡

ይህን ፈተና መቅረፍ የተቻለ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ለደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ጥሩ የሚባል ጊዜ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሕዝቡ ለሃይማኖቱ ጊዜ እንዳይኖረውና መንፈሣዊነትንም በግልጽ የሚቃወም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በመላው ሀገሪቱ አገልግሎቶች እየተዳከሙ ሰንበት ትምህርት ቤቶችም እየተዘጉ መጡ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ጉባኤያት ተዘግተው ይቆዩ ዘንድ ፍቃዱ ስላልነበረ በሂደት ነገሮች ወደ ቀድሞው ቦታቸው መመለስ ጀመሩ፡፡ አንቀጸ ብፁዓን ሰንበት ትምህርት ቤትም 1974 ዓ.ም ተመልሶ እንደገና ተደራጀ፡፡

በ 1976 ዓ.ም ከምስካየ ሕዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ሰንበት ት/ቤት ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ የኮሚቴ መዋቅርና የተለያዩ አሠራሮችን ዘርግቶ መንቀሳቀስ ቀጠለ፡፡

            ሰንበት ትምህርት ቤቱ በሰበካ ጉባኤ መስተዳደር ጥሩ የሚባልና ምቹ ሁኔታዎች የነበረው ሲሆን በተለይም ከዚህ ሰንበት ትምህርት ቤት መሠረት መያዝ ጋር በአብነት የሚጠቀሱትና ሰንበት ትምህርት ቤቱም ከሚያነሳቸው አባቶች መካካል ኮ/ል እምላዕሉ አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው በዚያን ጊዜ የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰበሳቢ ነበሩ፡፡ ወጣቶች በሰንበት ትምህርት ቤት ተደራጅተው የሚገባቸውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አመራር ከመስጠት ባሻገር በግል ንብረታቸውና ሐብታቸው ሰንበት ትምህርት ቤቱን የሚደግፉ ፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችን የሚያሟሉ በቅርብም የሚከታተሉ አባት ነበሩ፡፡

በጊዜው ይህ ሰንበት ትምህርት ቤት ወርሃዊ በጀት ነበረው፡፡ ይህም በወቅቱ በየትኛውም አጥቢያ ተደርጎ የማይታወቅና ለሰንበት ትምህርት ቤቱም ትልቅ መሠረት የጣሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በቤተክርስቲያን አስተዳደር አካላት ተደማጭነትና ተቀባይነት የነበረው ሲሆን እንዲያድግና ትልቅ ደረጃም እንዲደርስ ጥሩ ሁኔታዎች የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ከሰማኒያዎቹ ጀምሮ እዚህ ቦታ ላይ ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ  (በቁምስና ስማቸው አባ ኃይለ ኢየሱስ ክንፈ ገብርኤል ይባሉ የነበሩት) በነበሩበት ጊዜና ወደ ራጉኤል ተዘዋውረው ከደብሩ ለታላቅ  ክብር ታጭተው እስከሄዱበት ቀን ድረስ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ጥሩ ደርጃ ላይ የነበረበትና ጥሩ እይታ የነበራቸው አባቶች የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡

ምስሎች

Shopping Basket