ብዙውን ጊዜ ወጣት ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ከብዙዎች ስሜት መረዳት እንደሚቻለው በኃጢአት ስንወድቅና በኛ ውስጥ ያለው ክርስቲያናዊ ማንነት ከሰዎች ሁሉ በተለየ መልኩ ቆሻሻ ሆኖና መስሎ ከታየን፤ ከቅድስት ቤተክርቲያን፤ ከጸጋው ግምጃ ቤት፤ ከምሕረቱ አደባባይ መራቅን እንደ መፍትሔ አድርገን እንወስዳለን፡፡ ምክንያቱስ ያልን እንደሆነ ጥንተ ጠላት
ዲያቢሎስ ሰዎችን የግሉ የሚያደርግበት ትልቁ ታክቲክ ቢኖር፤ አስቀድሞ ወደ ኃጢአት
እንገባ ዘንድ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት፤ ስሜትን ከኅሊና በላይ አድርጎ በመሾም ማዘዝ፤
አንተ/አንቺ ከማን ትለያለህ/ትለያለሽ፤ ይህን ኃጢአት እንኳን አንተ መምህራኑ፤ ቀዳሾቹ፤ ካህናቱ፤
መዘምራኑ ሁሉ የሚሠሩት አይደለምን? የምን ማካበድ ነው በርታ በማለት ይገፋፋሀል፡፡
ኃጢአትን ካሠራንና የሚፈልገውን ሁሉ ካስፈጸመ በኋላ ደግሞ ይህ ካንተ አይጠበቅም ነበር፡፡
ሁሉ በንጽህና በቤቱ ሲኖሩ አንተ ግን ቆሽሸሐል፤ ረክሰሀል፤ ዋጋም የለሕም፤ ጥፋትህን ደግሞ
አምላክህም፤ ቅዱሳኑም፤ ጓደኞችህም ወዳጅ ጠላትህም አውቀውብሀል፡፡ ስለዚህ አትሞኝ ኃጢአተኛ
ነህ ከደጁ ምን ትሠራለህ? አንተን ብሎ አስቀዳሽ፤ ቆራቢ፤አገልጋይ ስለዚህም ማንንም አታግኝ፤፤
መንፈሳውያን ወንድሞችህን ወይም እህቶችህን በመንገድም ካየህ ሽሽ፡፡ ሰላምም አትበላቸው
ይልሀል፡፡ ይህ እውነት በእኔ ወይ በአንቺ ወይም በእናንተ ላይ የታየ መንፈሳዊ ፈተና ነው፡፡ ውሸት
ነው ብለን ልንሸሸው የማንችለው ሐቅ ነው፡፡
ነገር ግን እናስተውል ይሁዳ አምላኩን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት በርካታ የመዳን እድሎችን
አሳልፏል፡፡ ለመታነቅ ሲነሳ ዛፏ ሸሽታዋለች፤ ንጹህ ደም አሳልፌ በመስጠቴ ተጸጽቻለሁ ሲል
የነገረውን ውሳጣዊ ልቡናና መልእክት ገድሏል፡፡ ይልቁንም ጸጸቱን ሄዶ የተናገረው ለጸሐፍት እና
ፈሪሳውያን፤ለቀራጮች እና ለነፍሰ ገዳዮች ስለነበር እንዳልነው ባንተ አልተጀመረም አይነት ስብከት
ሲሰብኩት ነው ወደ መታነቁ ነው የሮጠው፡፡ ምናለ ለቅዱስ ጴጥሮስ፤ ለቅዱስ ዩሐንስ፤ለቅዱስ
ያእቆብ እና ለሌሎቹ ወንድሞቹ ነግሮ ቢሆን? ተው ወንድሜ ንሰሐ ግባ ብለው የጴጥሮስን እንባ
ባላበሱት ነበር፡፡እንደ ዘኪዎስም ጌታችን ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል እንዳለ፤ ለይሁዳም መዳን
በሆነለት ነበር፡፡ስለዚህ ክርስቲያኖች፤ በሐጢአት ምክኒያት ከቅዳሴው፤ከማእጠንቱ፤ከደጀ
ሰላሙ፤ከጉባኤው ሽሹ የሚል የጠላት መልእክት እና ጥሪ ሲመጣ ከእኔ ሽሽ፤የምኖረው እኮ ይቅር
ባይ እና ከባቴ አበሳ በሆነው አምላኬ ቤት ነው ልንል ይገባል፡፡
ይህ ማለት ግን በመጽሐፈ ሲራክ የእግዚአብሔር ቸርነት ብዙ ነው እያልክ በሐጢአት ላይ
ሐጢአትን አታድርግ ሲራክ 5፡-1 እንደተባለ በቸርነቱ ላይ መዘባበት እንዳያመጣ ጥንቃቄ ማድረግ
ያስፈልጋል፡፡ቸርነቱ ለጽድቃችን ዋስትና እንጂ ሐጢአትን እየደጋገሙ እርሱ ይቅር ባይ ነው
እንድንል አይደለምና በማስተዋል ልንጓዝ ይገባል፡፡ስለዚህም ጠላት ሰይጣን በሐጢአት ሰበብ ከቤቱ፤
ከደጀ ሰላሙ፤ ከቅድስናው አውደ ምህረት ሊያርቀን እና የውስጥ ሰላሙ የተዛባ ብኩን ስብእናን
ሊያላብሰን በተነሳ ጊዜ፤ተው አንተ ሰይጣን ከእኔ ራቅ፤ሐጢአተኛም ብሆን አንድ ቀን
ያነጻኛል፤በቤቱም የምጸናው ለመንጻት እንጂ በጽድቄ አይደለምና ወዴት አልሔድም ልንለው
ይገባል፡፡
‘’ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብጹአን ናቸው፡፡ እውነት እውነት
እላችኋለሁ፤ ታጥቆ በማእድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል፡፡’’ ሉቃስ 12-፤37 እንዲሁም
‘’አቤቱ በውሐ ፈሳሾች ዳር እደተተከለች ፤ ፍሬዋን በየጊዜው እደምትሰጥ፤ቅጠሏም እንደማይረግፍ
ዛፍ ልሁን፡፡ የምሰራውም ሁሉ የከናወንልኝ’’ እንበል፡፡ መዝሙረ ዳዊት 1፤3፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡

