photo_2023-05-16_12-25-23

ልደታ ለማርያም

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል አደረሰን!!!

ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከተለዩ የተለየች፣ ከተመረጡ የተመረጠች ክብርት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በከበረች ቀን ግንቦት አንድ ቀን ተወለደች፡፡ የመወለዷም ነገር እንዲህ ነው፡፡ በጥሪቃና ቴክታ የተባሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፤ ባለጸጎች ቢሆንም ልጅ ግን አልነበራቸውም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቴክታ ሕልም አለመች፡፡ ለባሏም እንዲህ ስትል ነገረችው «በራእይ ነጭ ዕንቦሳ ከማሕፀኔ ስትወጣ፤ ያችም ዕንቦሳን እየወለደች እስከ ፮ ትውልድ ስትደርስ ፮ኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃ ደግሞ ፀሐይን ስትወልድ አየሁ» አለችው፡፡ (ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)         

ባሏ በጥሪቃም «ራእዩስ ደግ ነው፤ የሚፈታልን የለም እንጂ» አላት፡፡ በማግሥቱ ለሕልም ፈቺ ሔዶ ነገረው፡፡ ሕልም ፈቺውም «እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል፤ በሣህሉ መግቧችኋል» ብሎ ፮ቱ እንስት ጥጆች መውለዳቸው ፯ ሴቶች ልጆች እንደሚወልዱ፤ ፯ኛይቱ በጨረቃ መመሰሏ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት እንደሚወለዱ፤ የፀሐይ ነገር ግን እንደንጉሥ ያለ ይሆናል አልተገለጸልኝም ብሎ ነገረው፡፡ (ነገረ ማርያም)
በጥሪቃም ለሚስቱ ሔዶ የሕልሙን ፍቺ ነገራት፡፡ በዚያም ወር የመጀመሪያዋ ሴት ልጅ ተፀነሰች፡፡ በተወለደች በ፰ኛው ቀን ሄኤሜን አሏት፤ ወላጆቿም በሥርዓት አሳደጓት፡፡ እርሷም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ ባል አግብታ ሴት ልጅ ወለደች፤ የሄኤሜን ልጅም ዴርዴን ትባል ነበር፡፡ ዴርዴንም እንዲሁ አድጋ ቶና የምትባል ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ቶና ደግሞ ሲካርን ወለደች፤ሲካርም ሔርሜላን ወለደች፤ ሔርሜላም በሥርዓት አድጋ ባል ካገባች በኋላ ሐና የተባለች ልጅ ወለደች፤ሐና ማለትም በሃይማኖትና በምግባር የጸናች፤ በንጽሕና በቅድስና የኖረች ቡሩክት ክብርት ልዕልት ማለት ነው፡፡ የሐና ወላጆች ልጃቸውን በሥርዓት አሳደጓት፡፡ ለአካለ መጠን ስትደርስም ኢያቄም የተባለውን ጻድቅ ሰው አጋቧት፡፡ ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑም ኖረዋለወ። በዚያ ወራት የመካኖች መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና፡፡ እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር፡፡ እናም ባልና ሚስቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ፤ ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ሐሳባቸውን ተመለከተ፡፡ ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው፡፡

በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ፤ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት። ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች። ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች፡፡

ከዚህም በኋላ ሐምሌ ፴ ኢያቄም ለሐና ራእይ አየ፤ ነጭ ርግብ ፯ቱን ሰማያት ሰንጥቃ ወርዳ በራሷ ስታርፍ በቀኝ ጆሮዋ ገብታ በማኅፀኗ ስታድር አየ፤ ሐናም ለኢያቄም ፀምራ ሲያስታጥቀህ መቋሚያህ አብባ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ ብላ» ነገረቸው፡፡

ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን በዕለተ እሑድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀነሰች፡፡ በ፶፻፬፻፹፭ ዓመተ ዓለም በግንቦት ፩ ቀንም እመቤታችን ድንግል ማርያም ከሐና እና ከኢያቄም፡፡ በ፰ኛው ቀንም ስሟን ‹ማርያም› ብለው ሰየሟት፤ በዚህ ዓለም ካሉት ምግቦች ሁሉ ጣፋጭ «ማር» በመሆኑ እንዲሁም በገነት ካሉት ምግቦች ደግሞ «ያም»ን የሚያህል ጣፋጭ ባለመኖሩ «ማርያም» አሏት፡፡ ትርጓሜውም ‹እመቤት› ነው።  ‹ደግሞም ሀብታና ስጦታ› ማለት ነው፡፡ በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት ናትና።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን፤ አምላካችን እግዚአብሔር ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ይክፈለን!

ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *