photo_2023-04-13_14-25-05

ስለ እኛ የታመመውን ምን አንደበት ይናገረዋል?!

እጅግ ጥልቅ የጸሎት ሕይወት የነበረው፣ አካሉ አልቆ በአጥንቶቹ እስኪቆም ድረስ የሚጾመው ተሐራሚው ቅዱስ አባ ጳጉሚስ ከእለታት በአንዱ ቀን ይህን ተመለከተ፡፡ ቅዱሱ ዓርብ ዓርብ የጌታችንን ሕማማት እያሰበ ከእንባ ጋር አብዝቶ ይሰግድ ነበር፡፡ ከዓይኑ የሚወርደው እንባ ከሰውነቱ ወዝ ጋር እየተቀላቀለ ወደ መሬት በመውረዱ ምክንያት የሚሰግድበትን ቦታ አረጠበው፡፡ አባ ጳኩሚስም ይህን ወደ ጌታው እያመለከተ “ይኸው አንተን አገኝ ብዬ እንዲህ እደክማለሁ” ሲል ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜም መድኃኒታችን ለአባ ጳጉሚስ ተገልጦ “እኔም እንጂ ላንተ ብዬ እንዲህ ሆኜ ተሰቅያለሁ” በማለት በእለተ ዓርብ እንደ ተሰቀለ ሆኖ የተወጋ ጎኑን፣ የፈሰሰ ደሙን አሳየው፡፡ ቅዱሱም የጌታው ሕማም ከሕሊናው በላይ ሆኖበት ወድቆ ምሕረትን ለምኗል፡፡

+++++++++++++

ሕሊናቸው የክርስቶስን ሕማም ከማሰብ አቁሞ የማያውቀው አባ መብዓ ጽዮን መድኃኔዓለምን :- ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፡፡ ስለ ራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ሲሉ ለመኑት፡፡ ጌታም ‹‹መከራ መስቀሌን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መባዓ ጽዮንም ‹‹አዎ! አይ ዘንድ እወዳለሁ›› አሉት። ያን ጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረው ታየ፣ በራሱም ላይ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር። እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ታያቸው። ይህን የመድኃኔዓለም መከራ የተመለከቱ የጻድቁ ዓይኖችም ፈዝዘው እስኪጠፉ ድረስ ትኩስ እንባዎችን ሲያዘንቡ ኖረዋል።

‹‹ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ›› – ‹‹ኃይሌና መጠጊያዬ እርሱ ጌታዬ ነው!››

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
selam@dnabel.com

Tags: No tags

Add a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *